top of page

Reviews

ስለ መጽሃፉ የተሰጡ አስተያየቶች

መኣዛ ወርቁ

የ ክህይንት ደራሲና ዳይሬክተር

ሰውየው ከልቡ ሰው ነው

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነጥበብና አርት ማእከል ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ ቴዎድሮስ ቲያትርን እያዘጋጁ ነበር አሉ በ1956 ዓ.ም ። ሰውየው ተማሪ ሆኖ ግሩም ተዋናይ ነበርና ለትወና ተመርጦ እየተለማመደ ሳለ በተማሪዎች ማህበር አባልነቱ አለምአቀፍ የወጣቶች ጉባኤ ለመሳተፍ ወደሞስኮ መሄድ ይኖርበታል። የቲያትሩን ልምምድ ማቋረጥ ስለነበረበት የእሱን ተክለሰውነት ይዞ የሚጫወተውን ገፀባህሪ ተክቶት የሚሰራ ሰው መፈለግ ግድ ሆነ። ሰውየው ለልምምድ ወደስነጥበብና አርት ማእከል/የአሁኑ ባህል ማእከል ይመስለኛል/ ሲመላለስ ወጋየሁ ንጋቱን ያየው ስለነበረ ከእኔ ጋር ይቀራረባል ብሎ እንዲተካው ይጠይቀዋል። ወጋየሁ በደስታ ይቀበላል ። ጋሽ ተስፋዬም ተስማሙ። ወጋየሁ በቲያትሩ ስሙ ሲገን ሰውየውም በፓለቲካ ከፍ ያለ ቦታ ኖረው። የእጣ ፈንታ ነገር። በኋላ ሰውየው ሲገደል ወጋየሁ አምርሮ አልቅሶለታል ይባላል።

 

ይሄን ታሪክ የኢትዮጵያን ቲያትር ታሪክ ስማር አላገኘሁትም። በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ቲያትር የነበረው ድርሻ በሚገባ አልተሰነደም። ሰውየው በ1956 ለኮሌጅ ቀን በገበሬዎች ህይወት ላይ ያተኮረ ቲያትርም ፅፎ አቀረበ። ቲያትሩ በኢትዮጵያ አብዮትና የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ አንድ መሪ ቃል አበርክቷል- መሬት ላራሹ። በተለያየ ስም የገበሬዎችን ህይወት ለመቀየር እንቅስቃሴ ቢኖርም መሪ ቃሉን የፈጠረው እሱ ነው። ሰውየው። ብርሀነ መስቀል ረዳ።

 

ብረሀነመስቀል ረዳ /ሰውየው/ በኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ የማይረሳ ድርሻ የነበረው ሰው ነው። በተለያዩ መፅሀፎች ፣ጥናቶች ፣ትዝታዎች ደጋግሞ የሚነሳ የገዘፈ ማንነት ያለው ፤ የሚወሳ ፣ልብ የሚሰብር ሀቅ ያለው ሰው ነው። ታሪኩ እና ማንነቱ "ዳኛው ማነው ?" በሚለው መፅሀፍ ውስጥ ከቅርቡ ሰው ከባለቤቱ ከ3 ልጆቹ እናት ታደለች ሀይለሚካኤል ጥሩ ተደርጎ ቀርቧል። ከTower in the sky / ማማ በሰማይ /ቀጥሎ ስሜት በሚነካ ቅርበት የተፃፈ እውነት ነው። ታደለች ዝርዝር ታሪኮች ላይ ቆጠብ ያለች ብትሆንም የሰውየውን ሰብእና ለታሪክ ስላቆየች እናመሰግናታለን። ታሪኳ፣ሀዘኗ ፣ ግርታዋ ፣ታማኝነቷ ልቤን ነክቶታል። በመፅሀፍ እንደዚህ ካለቀስኩ ቆየሁ መሰለኝ በስሜታዊነት እንዲህ አልኩ ። " ባልኖርም በዚህ ሰው ግድያ እጄ ያለበት ያህል ይፀፅተኛል። ማለፉ ይቆጨኛል። የምወደው አይነት የታጋይ ነፍስ አለው። እሱን ያጣችውን ኢትዮጵያ ሳስባት እሱ እና በከንቱ ያጣናቸውን ትልልቅ ማንነቶች እናፍቃለሁ , , ,"

 

መአት ነገር ነው ያልኩት ፣ ብዙ ነገር ነው የሚሰጣችሁ መፅሀፉ , ,ስለዛ የአብዮት ዘመን ብቻ አይደለም ስለዚህ ውዥብርብር ያለ ጊዜ "የቱ ጋር የሳትነው? ከምን ተነስተን ነው እንዲህ የሆንነው? ብላችሁ ትብሰለሰሉ ከሆነ ፍንጭ ብጤ ይሰጣችኋል።

ግዴላችሁም ሁላችሁም ሀገራችሁን አንብቡበት።

 እንድርያስ እሸቴ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የፍልስፍና ፕሮፌሰር

ለኢትዮጲያ አዲሱ ትውልድ እና ስለዓለም ሕዝባዊ ትግሎች ጥናት ለሚያደርጉ ተማሪዎች እጅግ ጠቃሚ ንባብ ነው። እህታችን ታደለች የሰጠችው ሀቀኛ፣ ሚዛናዊ እና ልባዊ ምስክርነት ለሁላችንም ባለውለታ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።

ባህሩ ዘውዴ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የታሪክ ፕሮፌሰር ኢሚሬተስ

በድብቅ ይካሄድ የነበረው የብርሃነ መስቀልና ታደለች የፍቅር ሕይወት ሦስት ልጆችን አፍርቷል። እነሆ አሁን ደግሞ አራተኛ ልጃቸው በዚህ መጽሐፍ መልክ ተከስቷል። ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም የፍቅርና የትግል ሕይወታቸውን ሙሉ ስዕል ለማግኘት በእጅጉ ይረዳል። ስለሆነም በዘመኑ ከተጻፉ ትውስቶች መካከል ቁንጮ ሥፍራ ሊይዝ የሚገባው ትርክት እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ልዑል በዕደማርያም መኮንን

ኢትዮጵያ

ብርሃነ መስቀል በዳይ ወይንስ ተበዳይ? የዛን ትውልድ ውስብስብ ታሪክ አንድ ገጽታ ይዛልን አምባሳደር ታደለች ቀርባለች። በዳኛው ማነው? የዛን ትውልድ መስዋዕትነት በተለመደ ግልጽነቷና ሰብዓዊነት በተላበሰ አቀራረብ በጥሩ ቋንቋ ገልፃዋለች።

ማስረሻ ፈጠነ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የአካባቢና የዕፅዋት ሳይንስ ፕሮፌሰር ኢሚሬተስ

በንቃት ለተሳተፈችበት ትግል፣ በፅናት ለተቀበለችው የመከራ ዘመን፣ ለእምነትና ለፍቅር ለከፈለችው መስዋዕትነት የሚመጥን የታሪክም የስነ-ፅሁፍም ሰነድ::

ወ/ሮ እንጉዳይ በቀለ በባህር ዛፎች ጥላ ሥር መፅሐፍ ጸሐፊ

የታዲ ውብ የፍቅርና ሰፊ የፖለቲካ ትርክት ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ በአላማ መፅናት እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ሊያስከፍል መቻሉን ያሳያል ትምህርት ሰጪ እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ።

ሕይወት ተፈራ

ደራሲ ፡ "Tower in the Sky", "Mine to Win", "Mintewab"

የ ብርሃነመስቀል መሞት የአንድ ዘመን ፋጻሜ መሰለ፥፥

bottom of page